Skip to main content

Posts

Showing posts from 2012

ቂጥ የሌለው ደሞዝ!

የአባቴን ደሞዝ፣ ድሮ ድሮ ሳውቀው ለሙሉ ቤት ወጪ፤ በወር ሲቆጥበው ከባልደረባው ጋር፣ እቁብ እየጣለው ቤት ሠራ፣ እቃ ገዛ፣ ኣረ ምኑ ቀረው፡፡ እኔም ሥራ ይዤ፤ ሆንኩና ተከፋይ ህዝብ የሚያገለግል፣ የአባቱ ተከታይ፤ ምን ያደርጋል አሁን፣ ነገር ተቀይሯል በሥም እንጂ ደሞዝ፣ ሲወሰድ ይከሳል እንኳን ለቁጠባ፣ መች ለጉርስ ይበቃል! የኮስት ሼሪንጉ፣ የግብሩ ብዛት የዓባል የዓባይ፣ የመዋጮው ብዛት፣ ለቤተሠብ ጣጣ፣ ያለበት ትኩሳት የዘይት የስኳር፣ የክራይ ቤት ንረት ከሻይ ማኪያቶ፣ የሚቆረጠው ቫት የጂንስ መወደድ፣ የሠልባጅም ልብስ መጥፋት፡፡ ኣረ ምኑን ትቼ፣ ምኑንስ ላነሳው ብቻ ተቆራርጦ፣ ኪሴ ስለገባው ይናገር ፔሮሌ፣ ጠይቁት ዋሌቴን፣ አሱ ነው የነጣው፡፡ እንኳን እንዳባቴ፣ ትዳር አስመስርቶ ጎጆን አስቀልሶ፣ ቤት ሊሞላ ቀርቶ አይደለም ለእቁብ፣ መች ዋለቴስ ገብቶ፣ አረ መች ሊገባ፣ ገብቶስ ምን ፈየደኝ እንደ ድሮው ሆኖ፣ መች ተቀመጠልኝ፡፡ ለነገሩ እሱም እውነት አለው፣ ምን ማድረግ ይችላል ከሄደበት ልከው፣ ሳይደርስ ይጠሩታል ቂጥ የሌለው ደሞዝ ፣ መቼ ይቀመጣል፡፡ December 21/12/12 መታሠቢያነቱ ለደሞዝተኛ © አኒቲ

ለዳግመኛ ፍቅር!

የባጡን የቆጡን ማህላ እየማልኩልሽ ልሰቀል ነው ልሞት ብዬ ጎተጎትኩሽ ልብሽን ሸርሽሬ የእኔ የብቻዬ ትሆኝ ዘንድ አረግኩሽ፤ የት ይደርሳል ሲባል አይን ውስጥ ገባሁና እንደ በሬው ሆንኩኝ ቄራ ታየሁና፡፡ አንቺ እያለምሽኝ ያገባኛል ብለሽ ሳላገባሽ ቀረሁ መጥፎሽን አግዝፌ ቀስ ብዬ ሸሸሁ ጥሩሽን ሸሽጌ ገላ ጠረንሽን አሽቼ ብጠግበው፤ እውነት ለመናገር ዛሬ ላይ ቁጭብዬ ትላንትን ስለካ ‘በእጅ-ያለ-ወርቅ …..’ እንዳሉት፣ ውስጤ ይፀፅታል በሚዘው አይረካ፡፡ እስካሁን ብቆይም፣ ደብቄሽ ስሜቴን፣ አልሸነፍ ብዬ ሲያይሽ ልቤ እንደ አዲስ፣ ወጥተሽ ከጉያዬ፤ እንዳልሆነ ምንም፣ አንቺን ሲመለከት የሚያደርገው ነገር፣ እንደሆነ ውሸት፤ በእናቴ ምላለው፣ እየታገለው እንጂ፣ የልቡን መፀፀት ፊቴ-ይናፍቀዋል፣ ፊቴ ያስፈልገዋል፣ የያኔው ፈገግታ የያን ግዜው ስሜት፡፡ እውነት የኔ ፍቅር፣ እውነት ለመናገር ያዛኔን ሽርሽር የየያኔ ገላሽን፣ ለሊት እንኳ ሳይቀር፤ ቀንማ ምንላድርግ፣ አምረሽ እያየሁሽ ፈርቼ ተዋለሁ ለሊት ማን ከልክሎኝ፣ እኮመኩማለሁ የያኔው አልበሜን፣ ላይሽ ከፎቶዬ፣ እንደከሰረ ዓረብ አገላብጣለሁ፡፡ ዓይኔን በጨው ባጥብም፣ ባይሠማኝ ዩሉኝታ እድል ስጪኝ ውዴ፣ እስኪ ለአንድ ላፍታ፤ ልቤ ልብ ገዝቶ፣ ለመመራት መቷል፣ የይቅርታን ቦታ አጢኚው ደጋግመሽ፣ ይህን አቤቱታ፡፡ ገንፍሎ ሲያገረሽ ፣ ሆንሽና ስራዬ መጣሁ ያንቺ ጠላት፣ ሁለቴ ልማረክ፣ እጅ ወደላይ ብዬ ነጠላ አዘቅዝቄ፣ ቅንድቤን ላጭቼ፣ እያለቃቀስኩኝ ውስጥሽን ገድዬ፤ ከደሙ እንደነፃ፣ ለቅሶው ላይ ያቆመኝ ምክንያቱን እወቂ፣ በዳግመ-መውደድሽ፣ በ ዳግመኛው-ፍቅርሽ ፣  አቅሌን ስላጣሁኝ፤ እንደ እጣ ወጥ...

የማግብያ ፈተና (ለትዳር)

የድሮው ተማሪ የያኔ ጠብሼ ኦልድ ካሪኩለም በፍቅሬ አንግሼ፤ ለስሙ ተምራ ምሁር ተብላለች በዚያ የዋህ ዘመን ሥራ የተቀጠረች፤ እናላእሁ ታድያ አሁን በቀደም ለት ሥራ ቀይር ብላ ማንበብ ቢያስፈልጋት፤ በአንድ ቢሮ ፊርማ ጫማዋን ማንጠልጠል መስቀል ቢደብራት መዋሉን ጀመረች ቀኑን ሙሉ ስትዞር እንጀራ ሲያዞራት፤ ለሷ የሚመቻት የምታውቀው ቢኖር የአዲስ ዘመን እትም አልያም ሪፖርተር፤ ethio-jobs ብል አታርፈው ነገር ተሰታ ትውላለች ከአራትኪሎ ደጃፍ እስከ ታች ለገሀር ለብይ ጫወታ ሲንፏቀቅ እንደዋለ ጨቅላ ህፃን በሠፈር እማስታወቂያ ደጅ ከጋዜጦች መንደር፤ ሼም ደግሞ የላትም ሁሌም ትዝታለች ትምህርት ድሮ ቀረ በኛ ግዜ እያለች፡፡ እውነት ለመናገር የትምህርቱ ጥራት የያኔ ይሻል ነበር፤ ቅሉ ምን ያደርጋል ታበሳጨኛለች IT አታርፍም ታሳዝነኛለች፤ Technology ነገር ያጥወለውላታል Computer ስታይ ነስር ይነስራታል፤ እንኳን እና facebook አንድ email የሌላት ግራ ነው ሚገባኝ ዘወትር ሳስባት፤ እንደ እኔ እንዳትሆኑ ህይወቴን ያያቹ እናም ጨምሩበት በያዛቹት መስፈርት እንደዚህ ብላቹ፤ ለም ት ጠብሱት ጥብስ ለነጌ አጋራቹ ለሚስት ብቻ ሳይሆን ብሎም ለባላቹ የማግብያ ፈተና Computer Literate መስፈሪያ ይሁናቹ እጅጉን እንዲያምር እንዲዘልቅ ፍቅራቹ፡፡ Aniti Nov, 2012 For the girl lol

ሳላሀዲን ሰዓድ ካዋራኝ የተገለበጠ ኢንተርቪው

Invisible journalist asking question through Magnetic Force of the mind First Audition የእምነት ነፃነት መፅሄት የመጀመሪያው እትም በሆነው ቅፅ ፻ የእንግዳችን ፕሮግራም አምድ ላይ ተጋባዥ ያደረግነው የጭንቅ ቀን ደራሹ የብሄራዊ ቡድናችን አጥቂ ከሆነው ሳላሀዲን ሰዒድ ጋር ያደረግነውን አጭር ቆይታ እነሆ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ የእምነት ነፃነት መፅሄት ፡ ሳላሀዲን መቼም በዚህ አጭር ግዜ ውስጥ (ልምምድ ላይ እንደመሆንህ መጠን) ለቃለ ምልልሱ ፍቃደኛ ሆነህ ስለመጣህ እያመሰገንን በቅድሚያ በአንባቢዎቻችን ስም እንኳን በደህና መጣህ ለማለት እንወዳለን፡፡ ሳላሀዲን ፡ እንኳን ደህና ቆያችሁኝ፣ የመጀመርያ እንግዳም ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡ ጥያቄ ፡ ሙስሊም እንደመሆንህ መጠን የመጅሊስ ምርጫ በቀበሌ መባሉን እንዴት ነበር ያየህው? ሳላሀዲን ፡ በግልምጫ፡፡ ጥያቄ ፡ ለምን? ሳላሀዲን፡ ምክንያቱም ድርጊቱ በመረብ ኳስ ሜዳ ላይ ጎል ተክሎ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያን የመጫወት ያህል ነው፡፡ ጥያቄ፡ የመንግስት አካላት ምርጫው በቀበሌ መሆኑ ህገመንግስቱን አይፃረንም ባዮች ናቸው አንተ ምን ትላለህ? ሳላሀዲን፡ እግር ኳስ ተጫዋች ስለሆንኩ የመረዳት አቅም የለውም በእግር ማሰብ አይደለም እንደማትለኝ እያመንኩ፡፡ ይህ ቀላል ጥያቄ ነው በሚቀጥለው ምርጫ 2007 የመንግስት ተወካይን ለመምረጥ የሀገሪቱ ህዝብ በመስጊድ እና በቤተክርስታን ማከናወን እንደሚችል ቃል ከገቡና በምርጫ ቦርድ ወይም በፓርላማው እንደ አንድ ፖሊሲ ካፀደቁት ምንም ችግር የለውም ባይ ነኝ፡፡ ጥያቄ፡ በሌላ መንገድ እምነት እና ፖለቲካን (ሰርግና ሞት አንድ ነው ጨፍር ምንድነው) እንደሚለው የ...

አንድ ነና

አንተ ረጅም ሎጋ እኔ አጭር ፉንጋ አንተ ሃብታምና አዋቂ እኔ ደሃ ዜጋ ሌቱን የማድር ያለንቅልፍ ቀኑን የምውል ስፈጋ ዓለምን ስትዞር አንተ እረፍት የለም እኔ ጋ አሁን ግን በቅቶኛል ምሬት ካናቴ ወጥቷል የ “አንድ ነን” ዲስኩርህ ሳያንሰኝ ዝምታዬ ጮሆብኛል ሞፈርና ቀንበሬ  እንኳ ድምጽ አውጥተው ወቅሰውኛል ውሸትህን ችዬ  ስኖር አይተው “ደንቆሮ ነህ ወይ” ብለውኛል እናማ ባልንጀሬ ሩቅ ሆነህ  የደለልከኝ እዚህ ኖረህ የራቅከኝ እስቲ ቼክህን አውሰኝ ከመልክህም ትንሽ ቸረኝ ትዳርህም ዛሬ ከኔ ትደር ገላዬን ካልጋህ ላኑር ላሳርፍ የዛለ ወገቤን ልጠግን ስብራቴን አንተ ደግሞ ኑር ኑሮዬን ተረከበኝ ስራዬን “ለምን”ን ምን አመጣው “አንድ ነና” ጓዴ ፈጠራዬም አይደል ያንተው ነው ዘመዴ ክረምት ከበጋ ይህን አይደል የሰበከኝ “ሁለት ነን” ስልህ “አይ አንድ ነን” አይደል ያልክኝ እንግዲህ ድህነቴን ቻለው መከራዬን ተሸከም እኔ ድሎትን ልልመድ ህመሜንም ላሣክም እኔ ልጆቼን ላስተምር አንተ እረኞችን ውለድ እኔ ከቢሮህ ልዋል አንተ ከብቶቼን ማግድ አንተ ቦርዴ ከጓደኞቼ ተጋራ እኔም ከመጠጦችህ ልጎንጭ እየቀዳሁ “ቺርስ” ልበል አንዴ ከቢጫው አንዴ ከቀይ አልያም ከነጭ ኮረዶችን ሰብስቤ ከሳሎንህ እኔ ሺሻ ላቡን አንተ ግባ ከኩሽናዬ በኩበት ጭስ ታጠን ግራሜውን ተው ወንድሜ ይልቅስ አድምጠኝ ላንቺም ጥያቄ አለኝ እህቴ አንዴ ልብ በይኝ ያንተ ከኔ አንድ መሆን የኔን ሽክም ካላዘለ የነም አንቺነቴ ያንቺን ምቾት ካልታደለ አንድነታችን ታዲያ የቱ ጋር ነው ያለ? ግርማ ታደሰ መስከረም 2005

እማማ በላይነሽ

ዛሬ ምነው አኒቲ ወሬ አበዛ እንዳትሉኝ፡፡ መቀባጠር ነው ብላችሁ ከሆነም በዓመት አንዴ እንድቀባጥር ከፈቀዳችሁልኝ እሰየሁ ዝቅ ዝቅ ሳቅ ሳቅ እያላችሁ አብራችሁኝ ዝለቁ፡፡ መቼም በዝህች ዓለም ላይ ስንኖር፤ በዕለት ተዕለት ንሮአችን፣ ማለትም በቤታችን፤ በሰፈራችን፤ በትምህርት ቤት፤ በስራ ቦታ፤ ሌላም ሌላም ቦታዎች የሚያጋጥሙን ከንፈር አስለጣጭ፤ ጥርስ አስከፋች ገጠመኞች ሊኖሩን ግድ ይላል፡፡ እናላችሁ ቀጥዬ የማወጋችሁን ገ ጠመኝ ያካፈለችኝ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ስትሆን ግዜው ቢቆይም (ያኔ በየሰፈሩ እና በየ ስራ ስሩ ስለ ኤች.አይቪ ማስተማር ብርቅ በነበረ ወቅት) እኔ የሰማሁት በዚሁ ዓመት በመሆኑ ለራሴ ብቻ ለምን ልገረም ብዬ (ያው መቼም ከናንተ የምደብቀው ነገር የለኝምና) ላካፍላችሁ ወደደኩ፡፡ ቦታው ኦሮሚያ ክልል አንቦ ከተማ አከባቢ ይመስለኛል ባልዘነጋው፡፡ የምላችሁ ወዳጄ ስለ ኤች.አይ.ቪ. ኤድስ እና ስለ ኮንደም ለከተማው ሴት ማህበራት እንድታስተምር ትጋበዝና ወደ ስፍራው ታቀናለች፡፡ ትምህርቱ ተጀመረ ተሳታፊወቹ ሴቶች ሲሆኑ ያው መሪ መኖሩ አይቀርምና በመሀላቸው የተለያዩ ተሰሚነት ያላቸው የየእድር መሪዎች ይገኙበታል፡፡ ከነኚህም ሴት መሪዎች መካከል ይህን ፅሁፍ ለመፃፍ ያበቁን እማማ በላይነሽ ይገኙበታል፡፡ እማማ በላይነሽ በከተማው የእድር መሪ ብቻም ሳይሆኑ ተሰሚነት ካላቸው በጣት ከሚቆጠሩ ቆፍጣና እና ቀብራራ ወዛዝርት መሀል አንዷናቸው፡፡ ወዳጄ ማስተማሩን ቀጥላለች (በነገራችን ላይ እድሜዋ ገፋ ያለ ሲሆን ምንም እኩል ባይሆንም ወደ እማማ በላይነሽ እድሜ ሰፈር ከአስር እና አስራ አምስት አመታት ቀደም የሚል ነው)፡፡   መቼም ስለ ኤች.አይ.ቪ. ኤድስ እና ስለ ኮንደም ለማስተማር ከምንጠቀማቸው ነገሮች ውስጥ ሁለት ዋና...

እንቀርባለን!

           እንቀርባለን! የእንግሊዝ ሊግ ብቻ አፍጥጠን እያየን እኛ እንደምንችል በጭራሽ ዘንግተን በሩጫ ላዪ ብቻ ሁሉን ነገር ጣልን፤ ምንድነው መመካት ብቻውን በሩጫ ዘራፍ! እንቀርባለን እኛም በዓለም ዋንጫ፤ ህዝባችን ዪዘፍናል በአንድነት ተቃቅፎ "ኢትዮፒያ መመኪያ"ን ከፍ አረጎ ለፍፎ፤ ማን ያውቃል ዪታያል ፖስተር ተለጥፎ ሰላሀዲን ሰኢድ ዋንጫ ሲስም ታቅፎ፡፡ መታሰቢያነቱ ለሳለህዲን ሰኢድ  አኒቲ

ቻዪና እንዳታገቡ!

መፍታቱን ፈታሽ ኝ ትዳሬን በተንሽው የወለድሽ ል ኝን ልጅ በባዶ ቤት ጣልሽው ብሎ ቢሳካልሽ የፈለግሽው ነገር ጡት አጥቶ በእሪታ እንዲያለቅስ ነበር ነበር የፈለግሽው ሲጨንቀኝ ለመስማት እንድለማመጥሽ በጡት ማጣት ምክንያት ቻዪና ነኝ እወቂ ሲፈቱኝ ፈታለሁ እራሴ እያጠባሁ አሳድገዋለሁ ጡትሽን እሚተካ ሌላ ጡት ሰራለሁ፡፡ መታሰብያነቱ ነጭ ለሚያድኑ የወገኔ አናዳጅ ችኮች ዪሁንልኝ፡፡                                                           አኒቲ

አላረጀሁም አላረጅም

እርጅና አፍጥጦ፣ በግላጭ ቢመጣ ፊትን አጨማዶ፣ መልኬ ቢገረጣ፤ እጄን አልሰጠውም፣ ወደላዪ አንስቼ እኖራለሁ ገና፣ መች ጠገብኩ በልቼ፤ በብእሬ ጫፎች፣ እያልኩኝ ብኩራራ በልበ ሙሉነት፣ ብጨፍር ባወራ፤ ሳላስብ ሳላውቀው፣ ሚስጥሩም ቢገባኝ የአርጅና ወንድም፣ ሞት መቶ ወሰደኝ፡፡ መታሰብያነቱ  ለጋሽ ስብሀት ይሁንልኝ፡፡                                         አኒቲ