አንተ ረጅም ሎጋ እኔ አጭር ፉንጋ
አንተ ሃብታምና አዋቂ እኔ ደሃ ዜጋ
ሌቱን የማድር ያለንቅልፍ ቀኑን የምውል ስፈጋ
ዓለምን ስትዞር አንተ እረፍት የለም እኔ ጋ
አሁን ግን በቅቶኛል ምሬት ካናቴ ወጥቷል
የ “አንድ ነን” ዲስኩርህ ሳያንሰኝ ዝምታዬ ጮሆብኛል
ሞፈርና ቀንበሬ እንኳ ድምጽ አውጥተው ወቅሰውኛል
ውሸትህን ችዬ ስኖር አይተው “ደንቆሮ ነህ ወይ” ብለውኛል
እናማ ባልንጀሬ ሩቅ ሆነህ የደለልከኝ
እዚህ ኖረህ የራቅከኝ
እስቲ ቼክህን አውሰኝ
ከመልክህም ትንሽ ቸረኝ
ትዳርህም ዛሬ ከኔ ትደር
ገላዬን ካልጋህ ላኑር
ላሳርፍ የዛለ ወገቤን
ልጠግን ስብራቴን
አንተ ደግሞ ኑር ኑሮዬን
ተረከበኝ ስራዬን
“ለምን”ን ምን አመጣው “አንድ ነና” ጓዴ
ፈጠራዬም አይደል ያንተው ነው ዘመዴ
ክረምት ከበጋ ይህን አይደል የሰበከኝ
“ሁለት ነን” ስልህ “አይ አንድ ነን” አይደል ያልክኝ
እንግዲህ ድህነቴን ቻለው መከራዬን ተሸከም
እኔ ድሎትን ልልመድ ህመሜንም ላሣክም
እኔ ልጆቼን ላስተምር አንተ እረኞችን ውለድ
እኔ ከቢሮህ ልዋል አንተ ከብቶቼን ማግድ
አንተ ቦርዴ ከጓደኞቼ ተጋራ እኔም ከመጠጦችህ ልጎንጭ
እየቀዳሁ “ቺርስ” ልበል አንዴ ከቢጫው አንዴ ከቀይ አልያም ከነጭ
ኮረዶችን ሰብስቤ ከሳሎንህ እኔ ሺሻ ላቡን
አንተ ግባ ከኩሽናዬ በኩበት ጭስ ታጠን
ግራሜውን ተው ወንድሜ ይልቅስ አድምጠኝ
ላንቺም ጥያቄ አለኝ እህቴ አንዴ ልብ በይኝ
ያንተ ከኔ አንድ መሆን የኔን ሽክም ካላዘለ
የነም አንቺነቴ ያንቺን ምቾት ካልታደለ
አንድነታችን ታዲያ የቱ ጋር ነው ያለ?
ግርማ ታደሰ
መስከረም 2005

Comments
Post a Comment