Skip to main content

Posts

Showing posts from December, 2012

ቂጥ የሌለው ደሞዝ!

የአባቴን ደሞዝ፣ ድሮ ድሮ ሳውቀው ለሙሉ ቤት ወጪ፤ በወር ሲቆጥበው ከባልደረባው ጋር፣ እቁብ እየጣለው ቤት ሠራ፣ እቃ ገዛ፣ ኣረ ምኑ ቀረው፡፡ እኔም ሥራ ይዤ፤ ሆንኩና ተከፋይ ህዝብ የሚያገለግል፣ የአባቱ ተከታይ፤ ምን ያደርጋል አሁን፣ ነገር ተቀይሯል በሥም እንጂ ደሞዝ፣ ሲወሰድ ይከሳል እንኳን ለቁጠባ፣ መች ለጉርስ ይበቃል! የኮስት ሼሪንጉ፣ የግብሩ ብዛት የዓባል የዓባይ፣ የመዋጮው ብዛት፣ ለቤተሠብ ጣጣ፣ ያለበት ትኩሳት የዘይት የስኳር፣ የክራይ ቤት ንረት ከሻይ ማኪያቶ፣ የሚቆረጠው ቫት የጂንስ መወደድ፣ የሠልባጅም ልብስ መጥፋት፡፡ ኣረ ምኑን ትቼ፣ ምኑንስ ላነሳው ብቻ ተቆራርጦ፣ ኪሴ ስለገባው ይናገር ፔሮሌ፣ ጠይቁት ዋሌቴን፣ አሱ ነው የነጣው፡፡ እንኳን እንዳባቴ፣ ትዳር አስመስርቶ ጎጆን አስቀልሶ፣ ቤት ሊሞላ ቀርቶ አይደለም ለእቁብ፣ መች ዋለቴስ ገብቶ፣ አረ መች ሊገባ፣ ገብቶስ ምን ፈየደኝ እንደ ድሮው ሆኖ፣ መች ተቀመጠልኝ፡፡ ለነገሩ እሱም እውነት አለው፣ ምን ማድረግ ይችላል ከሄደበት ልከው፣ ሳይደርስ ይጠሩታል ቂጥ የሌለው ደሞዝ ፣ መቼ ይቀመጣል፡፡ December 21/12/12 መታሠቢያነቱ ለደሞዝተኛ © አኒቲ