ፍቅርዬ ናት ብዬ፣ ያለውል የያዝኳት
የውል ያለሆነችን፣ እኔም ሚስቴ ምላት
ባሌ የምትለኝ፣ የውል ባል ያልሆንኳት
ለሚቆጠር ዓመት፣ ከልቤ ያኖርኳት
እሷም የምትወደኝ፣ እኔም የምወዳት
ሽምቅቅ ያደርጋታል፤ ‘ትዳር!’ ብዬ ስላት፡፡
በፍቅር መንደሬ፣ ከትማ ምትወደኝ
‘እንጋባ!’ ስላት፣
በመስፈርት ሸብባኝ፤
ውስጤ ቦታ-የሌላት፣ መጣች ያልተመራች
በሥራ አጋጣሚ፣ ሦስቴ ከኔው የዋለች፤
በዛች ተብሰልስዬ፣ ብቀርባት በስንዝር
በአንዴ ሠልላ፣ የውስጤን ለትዳር
ግዜ ሳታባክን፣ ምንም ሳትፈቀር
ብላኝ እርፍ አለች፣ ቀለበት እንሠር
ፍየል እዚ. . . አልኩኝ፣ ዙሩ በጣም ሲከር፡፡
ለእኔዋ የታየኝ፣ እንደ እንቦሳ ጥጆች
ጠብታ እንደጠገበች፣ ጠግባ እየቦረቀች
ሳታውቅ በፍንጠዛ፣ ከደጇ እንደራቀች
መሮጡም ሲደክማት፣ ሲመሻሽ ታውቃለች፤
አቁማ መቦረቅ ፣ ርቃ ለመመለስ፣ ብታዘግም ወዲ
አይኖር ሚቀመስ፣ እናቷ ታልባለች፣ ተገዳ በጋዲ፡፡
እንደው የሠው ነገር፣ እኔንም ጨምሮ
በጋርዮሽ ሕይወት፣ ለመኖር ተባብሮ
በራስ መውደድ ጠኔ፣ ውስጣችን ተቋጥሮ፤
ሞልቶ የማይሞላን፣ አሸን ሺህ ፍላጎት፣ ስንከተል ላንደርስ
ለሠው ሠው ካልኖረ፣ የሚፈላለግ ልብ፤ ጎጆን መች ይቀልስ?
እሱ እሱን ሳስበው. . .
ሠው እንደ ጉንዳን ነው፣ ኋላውን አያይም፣ የፊቱን ያፈቅራል
ለትዳር ላይሆነው፣ የፊቱም የፊቱን፣ ዱካ ይከተላል፤
ሲመሽ በመጣደፍ፣ እንደለነገሩ ትዳር ይደረጋል
ዳሩ አድሮ ሳይቆይ፣ ንዝንዝ ቃጠሎ፣ ምሬትን ይፈጥራል፤
መቼ በዚ በቅቶት፣ ሠማኒያን ይቀዳል፣ ለፍሬም ይተርፋል
ሲፈቀሩ ሽሽት፣ ሳያፈቅሩ ትዳር፣ በጣም ይደብራል፡፡
©
አኒቲ ግንቦት, 2005

Comments
Post a Comment